Fana: At a Speed of Life!

ማንኛውም አካል ሐሳቡን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ተነጋግሮ መፍታት አለበት – መርማሪ ቦርዱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ማንኛውም አካል ያለውን ፍላጎትና ልዩነት ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ተነጋግሮ በመፍታት ለሕብረተሰቡ ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ሚናውን እንዲወጣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አስገነዘበ፡፡

የመርማሪ ቦርዱ አባላት ከማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አመራሮች እና ከሰሜን ሸዋ ዞን የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱም በአካባቢው የሚታየው አሁናዊ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ፣ በሰላም መደፍረስ ሂደት የተያዙ ተጠርጣሪዎች አያያዝና መረጃ አጣርቶ ለፍርድ የማቅረብ እንዲሁም የሰብዓዊ አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግረዋል።

በአካባቢው ማንኛውም አካል ያለውን ፍላጎትና ልዩነት ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ተነጋግሮ በመፍታት፤ ለሕብረተሰቡ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባ የቦርዱ አባላት ገልጿል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጠርጥረው የተያዙ ተጠርጣሪዎች መረጃቸውን የማጣራት ስራ ተካሂዶ እንደየ ወንጀሉ ክብደት ከተሃድሶ ስልጠና እስከ ፍርድ ቤት የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም የዞኑ አመራሮች አስረድተዋል፡፡

በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ መደበኛ የልማት ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ማሳወቃቸውንም የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በኮማንድ ፖስት ስር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ዘላቂ የሆነ ሰላምና ፀጥታ ከማረጋገጥ አኳያ ከአካባቢው የሕብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ወጣቶችን አደራጅቶ ስልጠና እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.