ብሄራዊ የምርምርና ኤክስቴንሽን ስርዓትን በግብርና ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዕውን ለማድረግ ይሰራል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሄራዊ የምርምርና ኤክስቴንሽን ስርዓትን በግብርና ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዕውን ለማድረግ እንደሚሰራ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፍ እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናማኩሎ ኮቪክ ጋር የኢትዮጵያን የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮገራም በምርምር ለመደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የሰብልና እንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሀብትን ለማሻሻል፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እና ስርዓተ ምግብ ተኮር ቴክኖሎጂዎችን ለማፍለቅ በጋራ እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖን ለመቋቋምና የግብርና ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ለመጠቀም በጥናትና ምርምር ለመደገፍ በሚያስችል ሁኔታዎች ላይም መምከራቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ባለፈው፣ በአሁኑና በወደፊቱ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎች ላይ ጥናትና ምርምር እንደሚደረግም ተጠቁመዋል፡፡
ብሄራዊ የምርምርና ኤክስቴንሽን ስርዓትን በግብርና ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዕውን ለማድረግ እንደሚሰራም ነው በውይይቱ ላይ የተገለጸው፡፡
የግብርና ሴክተሮችን ግንኙነት ለማጠናከር ብሎም በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ የግል ባለሀብቱን ለመሳብ ሁለቱ ተቋማት በጋራ እንደሚሰሩ ተጠቅሷል፡፡
የሚደረጉት ጥናትና ምርምሮች የግብርናውን አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን፣ የአነስተኛ መስኖ ልማትና የምግብ ስርዓትን ከማሻሻል አኳያ እንደሚከናወኑም ተመላክቷል፡፡
ማንኛውም የግብርናውን ዘርፍ የሚደግፍ ፕሮጀክት ወይም ፕሮግራም ስራ ከግብርና ሚኒስቴር የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ጋር የተናበበ ሊሆን እንደሚገባውም በውይይቱ ተገልጿል፡፡