አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከቱርክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መከሩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተመራው ልዑክ ከቱርክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡርሃኔትን ዱራን ጋር ተወያይቷል፡፡
ምክክሩ፥ ሠባተኛውን የኢትዮጵያ-ቱርክ የፖለቲካ ምክክር አስመልክቶ እንደሆነ ተነስቷል፡፡
በምክክሩ ወቅትም አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዱራን፥ በሀገራቱ ሁለትዮሽ ግንኙነት፣ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮችን ዳስሰዋል፡፡
ምክክሩ በሀገራቱ መካከል ያለውን ቅርበትና ትብብር በተለያዩ ዘርፎች የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ መንገድ የሚከፍት እንደሆነም ነው የታመነበት፡፡
በዚህም ሀገራቱ በኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ትምህርትና ባህል ዙሪያ ያለውን ትብብርና አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የተካሄደው ምክክር ሀገራቱ ሁለንተናዊ ትብብርና ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያላቸውን አጋርነትና ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ አንካራ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።