Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል በ321 ሚሊየን ብር በጀት የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በ321 ሚሊየን ብር በጀት የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ሊገነባ መሆኑን የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።

የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የግንባታ የውል ስምምነቱን የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ዲኒ ረመዳን እና የፀሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀበን ረዘነ ተፈራርመዋል።

አቶ ዲኒ ረመዳን በወቅቱ እንደገለጹት÷ ሐረርን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ፅዱና ምቹ የማድረግ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ከዚህ አኳያ ባለስልጣኑ በከተማው ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች የመጸዳጃ ቤት ገንብቶ ለአገልግሎት ከማብቃት ባለፈ ሌሎች የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በከተማው ከሚገኙ መኖሪያ ቤቶች፣ ተቋማትና ከሌሎች መጸዳጃ ቤቶች የሚወጡ ፍሳሽ አወጋገድ ጋር በተያያዘ ውስንነት እንደሚታይና በህብረተሰቡ ዘንድም ቅሬታ ሲያስነሳ ቆይቷል ብለዋል።

ችግሩን ለማቃለል በ321 ሚሊየን ብር በጀት በክልሉ ሶፊ ወረዳ ሐረዌ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

አቶ ሀበን ረዘነ በበኩላቸው የጣቢያውን ግንባታ በ12 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ ማስገንዘባቸውን የክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.