በርካታ የአውሮፓ ሃገራት ድንበሮቻቸውን እየከፈቱ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ሃገራት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ጥለውት የነበረውን ክልከላ ማላላት ጀምረዋል።
በሃገራቱ ከዛሬ ጀምሮ ካፌና ሬስቶራንቶችን ጨምሮ፥ ሱቆች፣ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚጀምሩ ሲሆን፥ ድንበሮቻቸውን ክፍት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።
በእንግሊዝ ሱቆች ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈቱ ሲሆን፥ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትም ከዛሬ ጀምሮ ለተጠቃሚዎች ክፍት ሆኗል።
በሃገሪቱ የህዝብ ትራንስፖርት ተገልጋዮች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ግዴታውን ለማስተግበርም የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 3 ሺህ አባላት ያሉት ተቆጣጣሪ ቡድን ተቋቁሟል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሃገራቸው በቫይረሱ ላይ የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባለች ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከዛሬ ጀምሮ ከአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ለሚገቡ መንገደኞች ድንበሯን ክፍት ማድረጓን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ምግብ ቤቶች እና ካፌዎች አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፥ ትምህርት ቤቶችም ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውጭ የዛሬ ሳምንት ወደ መማር ማስተማር ሂደት ይመለሳሉ ተብሏል።
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ቫይረሱ አሁንም ዳግም ሊመለስ ይችላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
በተያያዘም ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ስዊዘርላንድ እና ክሮሺያ ከዛሬ ጀምሮ ድንበሮቻቸውን ክፍት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ቼክ ሪፐብሊክ እና ግሪክም በተመሳሳይ ድንበሮቻቸውን ክፍት ያደረጉ ሲሆን፥ ኦስትሪያ በነገው ዕለት ድንበሯን ክፍት እንደምታደርግ ገልጻለች።
ስፔን ደግሞ የዛሬ ሳምንት ድንበሯን ለጎብኚዎች ክፍት አደርጋለሁ ብላለች።
ስዊድን እና ሉክዘምበርግ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ድንበሮቻቸውን ያልዘጉ ሃገራት ሲሆኑ፥ ጣሊያን ቀደም ብላ ድንበሯን መክፈቷ ይታወሳል።
ዓለም ላይ 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው፥ 433 ሺህ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ