Fana: At a Speed of Life!

በምስራቅ ኢትዮጵያ ለሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ኢትዮጵያ ለሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንና የሕዝብ ግንኙነት አመራር አባላትና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በድሬዳዋ ከተማ እየተሰጠ ነው።

የአቅም ግንባታ ስልጠናውን የብልጽግና ፓርቲ ህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ከድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጀው፡፡

በአቅም ግንባታ ስልጠናው የብልፅግና ፓርቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ኢብራሂም የሱፍ ተገኝተዋል።

በስልጠናው ከአፋር፣ ከሶማሌ፣ ከሐረሪ ክልሎች እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች የተወጣጡ የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ መሰረትም ‘’የገዢ ትርክት ግንባታ እና የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና’’ በሚል ርዕስ በአቶ አዲሱ አረጋ አማካኝነት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

አቶ አዲሱ ÷ኢትዮጵያ የጥንታዊ ታሪክ እና ስልጣኔ ባለቤት ብትሆንም በመንግስታት ፍላጎት ላይ በተንጠለጠሉ ትርክት ግንባታዎች ምክንያት ዘላቂና ቅቡልነት ያለው ስርዓተ-መንግስት መገንባት እንዳልቻለች አንስተዋል፡፡

በተለይም ፍፁማዊ አንድነት እና ፍፁማዊ ልዩነት ባላቸው ሁለት አካታችነት በጎደላቸው ተገዳዳሪ ትርክቶች ምክንያት ኢትዮጵያ የስልጡን ፖለቲካ ባህል ባለቤት መሆን እንዳልቻለች ነው ያስረዱት፡፡

ትርክቶቹን አስታርቆ ዘላቂ ሀገረ መንግስት መገንባት የዚህ ትውልድ ሃላፊነት እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

በሁለቱ ትርክቶች ምክንያት በብርቱ ተፈትና ዛሬ ላይ የደረሰችው ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ አካታች ከሆነ ትርክት ውጪ ፈፅሞ ነጠላዊ ትርክት መሸከም እንደማትችል መግለጻቸውንም የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

የብሔራዊ ትርክት በዋናነት ህብረ ብሔራዊነት የተከበረባት፣ ጠንካራ አንድነት ያላትና የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት በመሆኑ ለትርክት ግንባታው ስኬታማነት ሁሉም የድሻውን ማበርከት እንደሚገባው ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዙ ጠቁመው÷ለብሔራዊነት ትርክት ስኬታማነት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.