አቶ ሽመልስ አብዲሳ የ2017 በጀት ዓመት እቅዶች በተገቢው ሁኔታ እንዲተገበሩ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ ለ2017 በጀት ዓመት የተያዙ እቅዶች በተገቢው ሁኔታ እንዲተገበሩ አሳስበዋል፡፡
አቶ ሽመልስ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ከበቂ ዝግጅት እና ሰፊ ውይይት በኋላ መጽደቁን አንስተዋል፡፡
ዕቅዱ ኢንሼቲቮችን በተመለከተ ሁለት ባህሪያት እንዳሉት ጠቁመው÷አንደኛው ማስፋፋት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም በሥራ ላይ በሚውሉ አዳዲስ ኢንሼቲቮች የመጀመሪያ ደረጃ ምርት ማምረቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባለፉት ዓመታት በሥራ ላይ የዋሉትን በብዙ እጥፍ አስፋፍቶ በመፈፀም ላይ ያተኩራል ብለዋል።
ሁለተኛው ዕሴት መጨመር ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷እንደ አዲስ ወደ ሥራ የሚገቡ ኢንሼቲቮች ደግሞ በሥራ ላይ ያሉ ኢንሼቲቮችን ዕሴትና ውጤት መጨመር ላይ የሚያተኩሩ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ይህ ማለት ወደ ሥራ የሚገቡ አዳዲስ የጎጆ ኢንደስትሪ ኢንሼቲቮች በሥራ ላይ ያሉትን የግብርና እና የከተማ ግብርና ኢንሼቲቮች ምርት ላይ ዕሴት የሚጨምሩ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
አቶ ሽመልስ “ቃል ኪዳናችን በፍጥነት፣ በብዛትና በጥራት የተያዘውን ዕቅድ በከፍተኛ ትኩረት ማሳካት ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሠረትም በየደረጃ ያለው አመራር በሰፊ ውይይትና መግባባት የተቀመጠውን ይህንን አቅጣጫ መዋቅሩንና ፈፃሚውን በማዘጋጀት ያለ ምንም ማንጠባጠብ ተመሳሳይነት ባለው ሁኔታ ወደ ተግባር እንዲቀይር አሳስበዋል፡፡