በትጋት ከሠራን የበለፀገች ኢትዮጵያን በቅርቡ እናያለን – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትብብር ተግተን ከሠራን ለኑሮ ምቹ በሆኑ ከተሞች ውስጥ የበለፀገች ኢትዮጵያን የምናይበት ጊዜ ቅርብ ነው ሲሉ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ አስገነዘቡ፡፡
በ117 ከተሞች የሚተገበረው የከተሞች ማስፋፊያ ፕሮግራም የመጀመሪያ ምዕራፍ አፈፃፀም ማጠቃለያ እና የሁለተኛ ምዕራፍ የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ መድረክ በጂግጂጋ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
ሚኒስትሯ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ በ117 ከተሞች እየተተገበረ ያለው የከተሞች ተቋማዊና የመሠረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም 859 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደተመደበለት አስረድተዋል፡፡
የፕሮግራሙን ዓላማ ለማሳካት በተከናወነ ሥራ 2 ሺህ 599 ኪሎ ሜትር በጌጠኛና ጠጠር መንገድ መገንባቱን ጠቁመው÷ ከ1 ሺህ 116 በላይ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ሼድና የገበያ ማዕከላት መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ከ286 ሔክታር በላይ የፓርክና አረንጓዴ ልማት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
ከ915 ሺህ 244 በላይ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አመላክተው÷ ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢም በ2012 በጀት ዓመት ከነበረበት 6 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እስከ 2015 በጀት ዓመት ድረስ 13 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር መድረሱን ነው የተናገሩት፡፡
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተደድር ሙስጠፌ መሐመድ በበኩላቸው÷ ከለውጡ ወዲህ በርካታ የመሰረተ-ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን በመግለጽ ለከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ምስጋና አቅርበዋል::
በቤዛዊት ከበደ