የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የ2016 ክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የ2016 ክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ 3” በሚል መሪ ቃል ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ የክልሉ የ2015 በጀት ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አፈጻጸም ግምገማ፣ ቀጣይ አቅጣጫ እንዲሁም የችግኝ ተከላና የአረጋውያን ቤት በማደስ እንደሚከናወን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)፣ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን ዋና አስተዳዳሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።
በዕለቱም ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በሚዛን አማን ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ሥራ አስጀምረው፤ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስን ጨምሮ ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።