የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ማሻሻያ አዋጅ ጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የምርጫ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅን አጸደቀ።
በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ የማሻሻያ አዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የአዋጁ መሻሻል በትጥቅ ትግል ስልጣን መያዝ የሚፈልጉ ሃይሎች ህጋዊና ሰላማዊ አማራጭን እንዲከተሉ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሰላምን ለማፅናት የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ አስፈላጊ የሆነ ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሃይልና በጠመንጃ ችግሮችን ለመፍታት መሞከር ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ የለውጡ መንግስት ለሰላማዊ አማራጮች በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ባህልን ለማሳደግ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻልና በትጥቅ ትግል የሚሳተፉ ቡድኖች ወደ ህጋዊ መንገድ እንዲመጡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርም አንዱ ትኩረት መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በተለያየ ምክንያት ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ቡድኖች ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል።
የትጥቅ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ያነሱት የምክር ቤቱ አባላት የማሻሻያ አዋጁ በአገሪቷ ሰላምን ለማፅናት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር የማሻሻያ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።