በአዲስ አበባ ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ልየታ በስኬት መጠናቀቁ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ላለፉት ሰባት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በቆየው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ልየታ የአዲስ አበባ የምክክር አጀንዳ ተለይቶ ዛሬ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
በመዲናዋ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በጋራ መክረው በቀጣይ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ሊመከርባቸው ይገባል ብለው ያመኑባቸውን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ለኮሚሽን ምክር ቤቱ ማስረከባቸውን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገልፀዋል።
ባለድርሻ አካላቱ በአምስት ቡድን ተከፍለው ሲመክሩ መቆየታቸውን አስታውሰው÷ በየቡድኑ የቀረቡ የአጀንዳ ሃሳቦችን በማጠናከርና በማደራጀት እንደ ሀገር ላሉብን ችግሮች መንስኤ ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ለመለየት ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል።
አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባሩ በያገባኛልና ሀገራዊ መንፈስ የተከናወነ በመሆኑ አለመግባባቶችን በመነጋገርና በምክክር ለመፍታት ለምናደርገው ረጅም ጉዞ አንድ ርምጃ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ያደረገውን የአጀንዳ ልየታ ተግባር በቀጣይ በመገምገምና ክፍተቶች ላይ እርምት በመውሰድ በተመሳሳይ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፣ በክልሎች፣ በፌደራልና በዳያስፖራ ደረጃ ሂደቱ አንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡
የእነዚህ አካላት አጀንዳዎች ከተሰበሰቡ በኋላ ከኮሚሽኑ ም/ቤት በአዋጅ በተሰጠው ተግባርና ሀላፊነት መሰረት አጀንዳዎችን የመቅረጽ ተግባር ያከናውናል ነው የተባለው፡፡
ይህ ሂደት ሲጠናቀቅም በሀገራዊ ጉባዔው ላይ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች ለሕዝብና ለባለድርሻ አካላት ይፋ እንደሚያደርግ ነው የተመላከተው፡፡
በታሪኩ ለገሰ