Fana: At a Speed of Life!

የመጀመሪያው የአፍሪካ የባዮቴክኖሎጂ ጉባኤ በመዲናዋ መካሄድ ጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የመጀመሪያው  የአፍሪካ የባዮቴክኖሎጂ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት እዉን ለማድረግ ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

መንግስት በባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የጉባኤው ዋነኛ ዓላማም ለአፍሪካ ሰፊ እና ዓለም አቀፋዊ የባዮቴክኖሎጂ ማህበረሰቦች መድረክ መፍጠር መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ÷አፍሪካ እያጋጠሟት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የባዮቴክኖሎጂ ሳይንሶች ሚና፣ እየተፈጠሩ ያሉ የባዮቴክኖሎጂ ጉዳዮችና ተግዳሮቶች ላይ ለመወያየት ያስችላልም ተብሏል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የባዮቴክኖሎጂ ሳይንስ እና ሌሎች እድገቶች ዙሪያም እየተሰራ ያለውን ስራ ለማስተዋወቅ መድረኩ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ነው የተባለው፡፡

በጉባኤው ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች እና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ሶሳይቲ ከሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት ይካሄዳል።

በይትባረክ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.