Fana: At a Speed of Life!

ለዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ከ128 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያለው የሕክምና ግብዓት ለማቅረብ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል የሚውል በ128 ሚሊየን 156 ሺህ 898 ብር የሕክምና ግብዓት ለማቅረብ ስምምነት ፈረመ፡፡

ግሩፑ ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ጤና ቢሮ እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድረጅት ጋር በፈጸመው የሦስትዮሽ የመግባቢያ ሠነድ መሠረት÷ ለሦስት ዓመት የሚሆን የሕክምና ግብዓት ድጋፍ ያደርጋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት÷ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለጤናው ዘርፍ የሚያደርገው ድጋፍ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ያሳያል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማኅበራዊ ኃላፊነት እና ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር አሊ ሱሌይማን በበኩላቸው÷ ተቋሙ በበርካታ ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ በመሳተፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልፀው፤ በጤናው ዘርፍ ያለውን አጋርነትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በመንግሥት ብቻ ሊሸፈኑ የማይችሉ ጉዳዮች ስላሉ ሌሎችም ድጋፍ በማድረግ ሕዝባዊ እና ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደምም ለማዕከሉ 40 ሚሊየን ብር የሚያወጡ 10 የኩላሊት ዕጥበት ማሽኖችን ከነግብዓታቸው ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው÷ ሁሉም ዜጋ ለተቸገሩ ወገኖች በመድረስ የበጎነት ተግባር ላይ መሳተፍ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ሰለሞን ንጉሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የሕክምና ወጪ የግሉ ዘርፍ ድጋፍ ማድረጉ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለጤና ዘርፍ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው÷ ተቋሙ ያደረገውን ድጋፍ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በልዩ ሁኔታ በአጠረ የጊዜ ሒደት ግዥውን ለመፈፀም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.