ኢትዮጵያ እና ሲንጋፖር ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሲንጋፖር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን በይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋገጡ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከሲንጋፖር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የሲንጋፖር ሪፐብሊክ ብሔራዊ ልማት እና ገንዘብ ሚኒስትር ኢንድራኒ ራጃህ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና ምቹ ሁኔታዎችን ያብራሩት አቶ አሕመድ÷ የሲንጋፖር ኩባንያዎች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ እና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጋብዘዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን÷ ሁለቱ ወገኖችም የሀገራቱን የፋይናንሺያል እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሠሩ ተስማምተዋል፡፡
ሚኒስትሯ በበኩላቸው÷ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በሲንጋፖር ላደረገው ጉብኝት አድናቆታቸውን ገልጸው የሀገራቱን የፋይናንስ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚና ፋይናንስ ዘርፍ ዕውቀትና ልምድ ለመለዋወጥ ቃል የገቡ ሲሆን÷ የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከርም ከሁለትዮሽ አጋርነት በተጨማሪ የባለብዙ ወገን ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡