አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው የልዑካን ቡድን ከጅቡቲ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ ሙሳ ደዋሌና ከንግድ ምክር ቤቱ አባላት ጋር ተወያየ።
አቶ ሽመልስ ሁለቱ ሃገራት ካላቸው ጥብቅ የንግድና የቢዝነስ ትስስር አንጻር የኦሮሚያ ክልል የቢዝነስ ማህበረሰብ በዚህ ሰፊ ዕድል በንቃት በመሳተፍ ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
አቶ ሽመልስ የጅቡቲ ባለሃብቶች በክልሉ ባለው ሰፊ የኢንቨስትመንት ሃብት ላይ በመሳተፍ ራሳቸውንና የሃገራቱን ህዝቦች ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጅቡቲ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሱፍ በበኩላቸው የጅቡቲ ባለሃብቶች በክልሉ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል።
በቀጣይም የጂቡቲ ባለሃብቶች በአዳማ ከተማ በሚካሄደው የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ኮንፈረንስ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመላክታል።
በውይይቱ ወቅት በእርሻ፣ በከብት ማድለብና በቱሪዝም መስክ ያልተነኩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ መሰማራት የሚያስችሉ ዕድሎች መኖራቸው ገለጻ ተደርጓል።