የዱርቤቴ – ቁንዝላ – ገለጎ – መተማ መንገድ ግንባታ አፈጻጸምን ለማሻሻል እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነቡትን የዱርቤቴ – ቁንዝላ – ገለጎ – መተማ ኮንትራት አንድ እና ሦስት መንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታወቀ፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞንን ከማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ጋር የሚያስተሳስሩት የኮንትራት – አንድ ዱርቤቴ – ቁንዝላ – ሻውራ – ፍንጅት እንዲሁም የኮንትራት – ሦስት የገለጎ – ገንደ ውኃ መንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመንገድ ግንባታዎቹ በጥቅሉ 260 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍኑ ሲሆን÷ የአዲስ አበባ – ደብረ ማርቆስ – ባሕርዳር እና የጎንደር – አዘዞ – መተማ ዋና መንገዶችን የሚያገናኙ ናቸው፡፡
አሁን ላይ የዲዛይን፣ የአፈር ቆረጣ እና ጠረጋ፣ የሰብቤዝ እንዲሁም የተፋሰስ እና የድልድይ ሥራዎች መሠራታቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር መረጃ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የአስፋልት ንጣፍ ለመጀመር የሚያስችሉ የክሬሸር እና የአስፋልት ፕላንት ተከላ መካሄዱ ተገልጿል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ÷ የዱርቤቴ፣ ይስማላ፣ ሊበን፣ ቁንዝላ፣ ዱባባ፣ ሽንፋ እና ሌሎች በርካታ ከተሞችን ደረጃውን በጠበቀ መንገድ እንደሚያገናኙ ተጠቁሟል፡፡
ይህም በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሽንብራ፣ ሰሊጥ፣ ጥጥ እና መሰል የአዝርዕት ምርት ውጤቶችን በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል፡፡