Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ በአቶ ታዬ ደንደአ ላይ የቀረቡ ምስክሮችን ቃል ሰማ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤቱ በቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ታዬ ደንደአ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የሁለት ምስክሮች ቃል ሰማ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት÷ ባለፈው ቀጠሮ አቶ ታዬ “የጻፍኩት ጽሑፍ ፕሮፖጋንዳ አደለም፣ ወንጀል አልፈጸምኩም” በማለት የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ምስክር እንዲሰማ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ጥያቄ መነሻ መሰረት ዛሬ የምስክሮችን ቃል አዳምጧል።

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የምስክር ጭብጥ በችሎት ካስመዘገበ በኋላ የሁለት ግለሰቦች የምስክር ቃላቸው ተሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የተሰሙ ምስክሮችን ቃልና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ ታዬ ደንደአ ላይ ሶስት ክሶችን አቅርቧል፡፡

አቶ ታዬ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ሆነው ሲሰሩ የሀገር፣ የመንግሥትና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅና ማረጋገጥ ሲገባቸው፤ ይህን ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኖችና የፀረ-ሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ ፕሮፓጋንዳ መልዕክቶችን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ሲያስተላልፉ ነበር የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም ፈቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ ታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ መሳሪያ፣ 2 የክላሽንኮቭ ካዝና፣ 60 የክላሽንኮቭ ጥይቶች ተገኝተዋል የሚል ክስም መቅረቡ ይታወሳል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.