አገልግሎቱ በተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ጋር በኢ አር ፒ ፕሮጀክት ትግበራ ላይ እየመከረ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን የተበታተነ የአገልግሎት አሰጣጥ በማቀናጀት ወጥ የሆነ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር እንደሚያስችል የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል፡፡
በ2015ዓ.ም በ9 ሚሊየን ዶላር በይፋ መጀመሩን አስታውሰው÷ አሁን ላይ በዋናው መስሪያቤት፣ በአዲስ አበባ ቁጥር 1 እና 2 ቅርንጫፎች፣ በአዳማ እና ሐዋሳ ቅርንጫፎች እየተተገበረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም በቀሪ ቅርንጫፎች አገልግሎቱን ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በ19 ቅርንጫፎች ከ1 ሺህ በላይ መድኃኒቶችን፣ የሕክምና መሳሪያዎችን እና የቤተ-ሙከራ ግብዓቶችን ለጤና ተቋማት እያቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ