በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች የልማትና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እየተጎበኙ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማትና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን እየጎበኙ ነው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) እና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ርስቱ ይርዳው በጎደር ከተማ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
በተጨማሪም በክረምቱ ወራቶች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሊተከሉ የተዘጋጁ የዛፍና የፍራፍሬ ችግኞችን ዝግጅት በችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ተገኝተው እየተመለከቱ ይገኛሉ።
በከተማው የኢንዱስትሪ መንደሮች ጨምሮ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በወጭና በተኪ ምርቶች የተሰማሩ ባለሃብቶችን የምርት ሒደት እንደሚጎበኙም ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተስፋየ ይገዙ በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን እየጎበኙ ነው።
በከተማው የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችና ሌሎች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችንም እየጎበኙ መሆኑ ተመላክቷል።
በተመሳሳይ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪና የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በደሴ ከተማ የልማት ስራዎችን እየጎበኙ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
በጉብኝቱ ወቅት ህብረተሰቡን ጭምር በማስተባበር በከተማው የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የአስፓልት መንገድ፣ መናኸሪያ፣ ድልድይ፣ የአስተዳደር ህንጻና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች ግንባታቸው እየተጠናቀቀ እንደሆነ ተጠቁሟል።