ጠረፍ አካባቢ የሚካሄደው ንግድ የወጪ ንግዱን ሊያበረታታ በሚችል መልኩ እንዲከናወን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠረፍ አካባቢ የሚካሄደው ንግድ የወጪ ንግዱን ሊያበረታታ በሚችል መልኩ እንዲከናወን ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ልኡክ ጋር የጠረፍ ንግድን ማሳለጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ አቶ ካሳሁን ጎፌ÷ ኢትዮጵያ በምትዋሰንባቸው ሀገራት ጠረፍ አካባቢ የሚካሄደውን የጠረፍ ንግድ ህጋዊ ስርዓት በማበጀት የወጪ ንግዱን ሊያበረታታ በሚችል መልኩ እንዲካሄድ ለማስቻል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከጂቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከኬንያ ጋር የጠረፍ ንግድ የሚካሄድባቸውን መስፈርቶችና ቅድመ ሁኔታዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም ከኬንያ ጋር የሚኖረውን የጠረፍ ንግድ ስምምነት አስመልክቶ የሚቀሩ ጉዳዮችን ከአይኦኤም ጋር በመተባበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ዝግጁ ነን ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በውይይቱ ወቅት÷ በቀጣይ በኢትዮጰያ እና በጎረቤት ሀገራት ጋር የሚካሄደውን የጠረፍ ንግድ ለማጠናከርና ለማሳለጥ በሚቻልባቸው ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡