የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫ “ቢስት ባር” መከበር ጀምሯል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫ “ቢስት ባር” በድምቀት መከበር ጀምሯል።
ቢስት ባር ወደ አዲስ የዘመን ምዕራፍ መሻገር የሚበሰርበት ብኩርና ክብሩ ከፍ የሚልበት፣ አብሮነት የሚነግስበት እንዲሁም ለፈጣሪ ታላቅ ምስጋና የሚቀርብበት ባህላዊ እሴት ነው።
የቤንች ብሄር አባላት ፈጣሪ እህሉን ከበረዶ ከጎርፍና ከሌላ አደጋ ጠብቆ ፍሬ እንዲሰጥ በማድረጉ፣ ህዝቡ ሰላምና ጤና ሆኖ ወደ አዲስ የዘመን ምዕራፍ በመሻገሩ እና ከክረምት ጎርፍ ነጎድጓድና ጭቃ አልፎ የጸደይ ጸሀይ ያደመቀችው አዲስ ቀን በመምጣቱ ለፈጣሪ ምስጋና ያቀርባሉ።
ቢስት ባር ደስታና ፈንጠዝያ በቤንች ቀዬ የሚናኝበት አዲስ ተስፋ ከአዲስ ብርሃናማና ብሩህ ቀን ጋር አብሮ የሚወለድበት በዓል ነው።
ይህ በዓል ለዘመናት በቀደሙ አባቶች ሲከበር ኖሮ በተለያዩ ምክንያቶች በዓሉ ሳይከበር ለአያሌ አመታት ተቋርጦ ቆይቷል።
ቢስት ባር ከተቋረጠ ከረጅም ዓመት በኋላ በተደራጀ መንገድ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መከበር ጀምሯል፡፡
በዚህም የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫ “ቢስት ባር” በድምቀት መከበር የጀመረ ሲሆን÷ በነገው እለት በሚዛን አማን ከተማ አማን ሜዳ በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ይሆናል።