ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ መረባረብ ይገባናል – አምባሳደር ምስጋኑ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትብብር ተምሳሌት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ መረባረብ ይገባናል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተናገሩ፡፡
ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከዳያስፖራው ሀብት ለማሰባሰብ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር ከኢፌዴሪ ሚሲዮኖች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ÷ ወደ ማጠቃለያ ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ የሚገኘውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለፍጻሜ ለማብቃት የፐብሊክ ዲፕሎማሲና አድቮኬሲ እንዲሁም የሀብት ማሰባሰብ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናውም በበኩላቸው÷ ዳያስፖራው ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በዕውቀትና ክህሎት ሽግግር፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና አድቮኬሲ እና በሃብት ማሰባሰብ እያደረጋቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
ለ #ጽዱኢትዮጵያ ንቅናቄም ከዳያስፖራውና ከኢፌዴሪ ሚሰዮኖች ቃል የተገባውን ጨምሮ ከዕቅድ በላይ ከ45 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ በመቻሉ ምስጋና ቀርቧል፡፡
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማጠናቀቂያ ሀብት ለማሰባሰብ የተዘጋጀው ዕቅድም ቀርቦ ውይይት እንደተካሄደበት ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አምባሳደሮችም ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች የተጀመረውን የሀብት ማሰባሰብ ተግባር አጠናክረው ለመቀጠል እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡