የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫ “ቢስት ባር” እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫ “ቢስት ባር” የማጠቃለያ በዓል በሚዛን አማን ከተማ በአማን አየር ማረፊያ ሜዳ በድምቀት እየተከበረ ነው።
በበዓሉ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
ቢስት ባር ወደ አዲስ የዘመን ምዕራፍ መሻገር የሚበሰርበት ብኩርና ክብሩ ከፍ የሚልበት፣ አብሮነት የሚነግስበት እንዲሁም ለፈጣሪ ታላቅ ምስጋና የሚቀርብበት ባህላዊ እሴት ነው።
የቤንች ብሔር አባላት ፈጣሪ እህሉን ከአደጋ ጠብቆ ፍሬ እንዲሰጥ በማድረጉ፣ ህዝቡ ሰላምና ጤና ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሻገሩ እና ከክረምት ጎርፍ ነጎድጓድና ጭቃ አልፎ የጸደይ ጸሀይ ያደመቀችው አዲስ ቀን በመምጣቱ ለፈጣሪ ምስጋና ያቀርባሉ።
ቢስት ባር ደስታና ፈንጠዝያ የሚናኝበት አዲስ ተስፋ ከአዲስ ብርሃናማና ብሩህ ቀን ጋር አብሮ የሚወለድበት በዓል መሆኑ ተገልጿል።
በዓሉ በተለያዩ ምክንያቶች ለአመታት ተቋርጦ ቆይቶ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግንቦት 29 ቀን ጀምሮ እየተከበረ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በተስፋየ ምሬሳ