ጠ/ሚ ዐቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘታቸው ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ያላትን ተቀባይነት ያሳድጋል-ፖለቲከኞች
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሆናቸው ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ያላትን ተቀባይነት እንደሚያሳድገው ፖለቲከኞች ገለፁ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ እና አቶ ሌንጮ ለታ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሽልማቱ ኢትዮጵያ ስሟን በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረገ እና የዜጎቿን ክብር የጨመረ መሆኑን ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ይናገራሉ፡፡
ለዚህ የውጭ እውቅናም በሃገር ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመፍታት መደገም እንደሚኖርበትም ገልፀዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሚዛናዊ ለማድረግ የቤት ስራዎችን ማከናወን ይገባታልም ብለዋል፡፡
ሌላኛው ፖለቲከኛ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሰላም ተሸላሚ መሆን ቱሩፋቱ ለኢትዮጵያ መሆኑን ያነሳሉ።
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን የጭንቀት ጊዜ ለመቋጨት ለተወሰደው ወሳኝ እርምጃ የተሰጠ ዕውቅና መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ላሳዩት መልካም ተስፋ ሰጭ እርምጃዎች እና ላከናውኗቸው ትልልቅ ስራዎች ትኩረት የሰጠም ነው ብለዋል።
ሁሉም የፖለቲካ ሀይል የዜጎችን ስኬት በመልካም ጎን መመልከት ይኖርበታል የሚሉት ዶክተር ደሳለኝ፥ በልሂቃን በኩል ልዩነቶች ቢኖሩም የጋራ የሚያደርጉ በርካታ ጉዳዮች አሉ ነው ያሉት፡፡
አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው ሀገሪቱ ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ ቢሆንም ዓለም በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ተስፋዎች እንዳለው ያመላክታል ብለዋል።
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሃገር ውስጥ በርካታ የጀመሯቸው ጉዳዮች ስለመኖራቸው የሚናገሩት አቶ ሌንጮ፥ ስለኢትዮጵያ መጻኢ እጣ ፈንታ ሁሉም ተወያይቶ መስማማት አለብን ሲሉ ያነሳሉ።
መስማማት አለብን ሲባልም የሁሉም ፍላጎት ይመለሳል ማለት ሳይሆን ሰጥቶ መቀበልን ፖለቲከኞች መልመድ አለባቸውም ነው የሚሉት።
ይህ ከሆነም ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመሸጋገር ሂደቱ ፈጣን እንደሚሆን እና ለዚህም ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡
በበላይ ተስፋዬ