ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት 52 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት 52 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን ማጽደቁን የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት ባካሄደው 29ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው በሶስት ዘርፎች ተዘጋጅተው የቀረቡለትን 52 ብሔራዊ ደረጃዎችን ያፀደቀው።
ከፀደቁት ደረጃዎች ውስጥ 31 አዳዲስ ሲሆኑ 4 ደረጃዎች የተከለሱ፣ 17 ደረጃዎች በማስቀጠል በድምሩ 52 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን ማጽደቁን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዚሁ መሠረት ከፀደቁት የኢትዮጵያ ደረጃዎች ውስጥም በአካባቢ ጤናና ደህንነት የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ 22 አዲስ፣ 1 በክለሳ ፣ 12 በማስቀጠል በጠቅላለው 35 የኢትዮጵያ ደረጃዎች ተጠቃሽ ነው።
በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ 5 አዲስ፣ 5 በማስቀጠል በድምሩ 10 የኢትዮጵያ ደረጃዎች የፀደቁ ሲሆን፥ በመሠረታዊና አጠቃላይ የደረጃ ዝግጅት ዘርፍ4 አዲስ፣ 3 በክለሳ በድምሩ 7 የኢትዮጵያ ደረጃዎች መጽደቃቸውም ታውቋል።
በአጠቃላይ የፀደቁት የኢትዮጵያ ደረጃዎች በአሁኑ ወቅት በዓለምና በኢትዮጵያ በመስፋፋት ላይ የሚገኘውን ኮቪድ 19 በመከላከሉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ብሔራዊ የኮቪድ-19 አመራር ሰነድ እና ከሐገራዊ ጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ ጋር የተቃኙ መሆናቸውም ተገልፇል።
ይህም የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ከተቀመጡት የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር የተገናዘቡ፣ በደረጃው መሰረት ለሚያመርቱና ለሚያከፋፍሉ እንዲሁም ለሚጠቀሙ አካላት ከፍተኛ ሚና የሚኖራቸው፣ ከአመራረትና አጠቃቀም ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ጥራትን ከማሻሻልና ከማረጋገጥ አንፃር ለማምረቻ ኢንዱስትሪና ለንግድ የተወዳዳሪነትን አቅም ለማጎልበት ይረዳሉ ተብሏል።
ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ኢኖቬሽን እንዲሁም የቫይረሱን ባህሪ ለመመርመርና ለዕውቀት ሽግግር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸውም ነው የተገለፀው።
ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም የህብረተሰቡን ጤናና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ ጉልህ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ ተብሏል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።