ባለፉት 24 ሰዓታት 109 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው፤ 118 ሰዎች አገግመዋል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 5 ሺህ 102 የላብራቶሪ ምርመራ 109 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 630 መድረሱንም የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ ባወጡት ሪፖርት አመላክተዋል።
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ የእድሜ ክልላቸውም ከ1 እስከ 78 ዓመት የሆኑ 60 ወንዶች እና 49 ሴቶች ናቸው።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከልም 81 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 9 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 4 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 4 ሰዎች ከደቡብ ክልል፣ 3 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 3 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 3 ሰዎች ከአፋር ክልል እና 2 ሰዎች ከሐረሪ ክልል ናቸው።
በትናንትናው እለትም በቫይረሱ የ1 ሰው ህይወት ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን፥ ከጠቅላላው የላብራቶሪ ምርምራ ውስጥ 20 ናሙናዎች በአስክሬን ላይ የተደረገ መሆኑንና በዚህም የ45 ዓመት ኢትዮጵያዊ የአዲስ አበበ ነዋሪ ሴት የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባታል።
ይህንን ተከትሎም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 61 ደርሷል፡፡
በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት 118 ሰዎች (115 ከአዲስ አበባ እና 3 ከትግራይ ክልል) ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 738 ደርሷል።
ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ192 ሺህ 87 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 630 ደርሷል።
አሁን ላይ 2 ሺህ 829 ሰዎች በህክምና ላይ ሲሆኑ፥ ከእነዚህም ውስጥ 32 ሰዎች በጽኑ የታመሙ መሆናቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
እስካሁን በኢትዮጵያ 738 ሰዎች ከቫይረሱ ሲያገገሙ፤ የ61 ሰዎች ህይወት አልፏል፤ 2 ሰዎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።