Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ ውኃ የሚያርፍበት ቦታ የደን ምንጣሮ ለማካሔድ የፊታችን ሐሙስ የቦታ ርክክብ ይፈጸማል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 09 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውኃ በሚያርፍበት ቦታ ላይ የሚገኘውን የደን ምንጣሮ ስራ ለመጀመር የፊታችን ሐሙስ የቦታ ርክክብ እንደሚካሔድ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ።

የክልሉ የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም÷ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያውን ሃይል ማመንጨት የሚያስችለው ውሃ የሚተኛበት ቦታ ለማመቻቸት የደን ምንጣሮ ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል፡፡

ምንጣሮውን ከሚያካሂዱ 45 ኢንተርፕራይዞች ጋር ውል መገባቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ስራውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል ።

የምንጣሮ ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ሌሎች 25 ኢንተርፕራይዞች በተጠባባቂነት መመዝገባቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

ውሃው የሚተኛበት አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ለምንጣሮ የተዘጋጀ ሲሆን የፊታችን ሐሙስ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በክልሉ መንግስት መካከል ርክክብ ይካሔዳል ብለዋል ።

ለደን ምንጣሮ ስራው ከሚያስፈልገው 33 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ውስጥ በውሉ መሠረት ስራውን ለሚያከናውኑ ኢንተርፕራይዞች የሚተላለፍ 6 ሚሊዮን ብር የቅድሚያ ክፍያ መለቀቁንም ሃላፊው አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ ሳምንት የምንጣሮ ስራው በይፋ እንደሚጀመርም ነው ዳሬክተሩ  ያስታወቁት ፡፡

አቶ በሽር አያይዘውም ከ1 ሺህ 200 በላይ የክልሉ ስራ አጥ ወጣቶች በምንጣሮ ስራው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመው÷ ከሚያገኙት ገንዘብ 30 በመቶ በመቆጠብና ጥሪት በማፍራት ወደ ተሻለ ኢንቨስትመንት የሚሸጋገሩበት ሁኔታ መመቻቸቱን አስረድተዋል፡፡

የደን ምንጣሮ ስራውን የሚያካሂዱት ወጣቶች ስራውን በወቅቱ አጠናቀው ለማስረከብ ከወዲሁ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል፡፡

የግድቡን ምንጣሮ ከሚያካዱ ኢንተርፕራይዞች መካከል የአለማየሁና ዘላለም ምንጣሮ እና ጽዳት ኢንተፕራይዝ ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ መልካሙ በሰጡት አስተያየት÷ 26 የማህበሩ አባላት የደን ምንጣሮውን ስራ ለመጀመር በጉጉት እየጠበቁ ነው ብለዋል፡፡

በስራው የምንሳተፈው በዋነኝት የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት በማሰብ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም የሚደረገው ዘመቻ ግድቡን ከመጨረስ አያግደንም የሚሉት ሊቀመንበሩ በሥራችን ወቅት የሚያጋጥሙን ችግሮች ቢኖሩም እንኳን የህይወት መስዋእትነት ጭምር በመክፈል ሥራውን በወቅቱ ለማጠናቀቅ ጠንክረን እንሰራለን  ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.