Fana: At a Speed of Life!

የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የሚያስችል የብድር ስምምነት አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 33ኛ መደበኛ ጉባዔ የተጀመሩ የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የሚያስችል የብድር ስምምነት አዋጅ አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በጉባዔው በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለ2ኛው የከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት አዋጅ ነው መርምሮ ያጸደቀው፡፡

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ስምምነቱን አስመልክቶ እንደገለጹት÷ በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር የተገኘው 275 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ከወለድ ነጻ ነው፡፡

ስምምነቱ በፕሮግራሙ የተነደፉ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እና ያጋጠመውን የበጀት ክፍተት ለመሙላት የተደረገ የተጨማሪ የብድር ስምምነት ነው ብለዋል፡፡

ብድሩ በቀጣይ ሶስት አመታት ተግባራዊ የሚሆን እና በጅምር ላይ ያሉ የሁለተኛው የከተሞች የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡

ባንኩ በሚወስነው መሰረት ጥቅም ላይ እንደሚውል በመግለጽ ጥቅም ላይ ባልዋለው የብድሩ ገንዘብ ላይ በዓመት እስከ 0 ነጥብ 5 በመቶ የሚደርስ የግዴታ ክፍያ ሊከፈልበት ይችላል ብለዋል፡፡
ብድሩ የ6 አመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 አመታት ውስጥ ተከፍሎ ይጠናቀቃል ተብሏል።

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.