የ2017 ረቂቅ በጀት ሀገራዊ የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠልን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ነው -ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2017 በጀት ዓመት የቀረበው ረቂቅ በጀት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማረጋገጥና ያለፉት ዓመታት የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
ስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌደራል መንግስት የ2017 ረቂቅ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ሆኖ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መምራቱ ይታወቃል፡፡
ከጥቅል በጀቱ 451 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለመደበኛ፣ 283 ነጥብ 2 ቢሊየን ለካፒታል ወጪዎች እና 236 ነጥብ 7 ቢሊየን ለክልል መንግስታት የበጀት ድጋፍ የተመደበ ነው።
ረቂቅ በጀቱ ከ2016 በጀት አንጻር የ21 ነጥብ 1 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል።
የገንዘብ ሚኒስቴር በቀረበው የፌደራል መንግስት የበጀት ረቂቅ ዙሪያ በዛሬው ዕለት ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የገንዘብ ማኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የበጀት ረቂቁ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምን መነሻ በማድረግ በ2017 የተሻለ ለመፈጸም ያለመ ነው።
በጀቱ በአብዛኛው በሀገር ውስጥ ገቢ እንደሚሸፈንም ነው ለቋሚ ኮሚቴው ያብራሩት።
በጀቱ በተለይ ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ አምራች ዘርፎች ምርትና ምርታማነት መጨመር እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራን ለማስፋት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ሀገራዊ ወጪን በራስ አቅም ለመሸፍን እቅድ ተይዞ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይህን ግብ ለማሳካት የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ፥ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ከማዘመን ጀምሮ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ የ2017 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት የልማት ስኬቶችን ለማስቀጠል፣ ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋትና የዋጋ ንረት እንዲቀንስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላቸው፤ በጀቱ የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
የፋይናንስ ምንጩ ከብድርና እርዳታ ይልቅ የአገር ውስጥ ገቢን መሰረት ያደረገ መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የበጀት አፈጻጸሙ ጥብቅ ዲስፕሊን ያስፈልገዋል ያሉት አቶ ደሳለኝ÷ ለዚህም ገንዘብ ሚኒስትር ቁጥጥርና ክትትሉን ማጠናከር እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ከዛሬው ማብራሪያ በጀቱን የተመለከተ የውሳኔ ሃሳብ አደራጅቶ ለምክር ቤቱ ለማቅረብ በቂ ግብዓት መገኘቱ ተገልጿል፡፡