በተቀናጀ አሰራር የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታትና የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መስራት ይገባል – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተቀናጀ አሰራር የመሰረተ ልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እና የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
በክልሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ ተደራሽነት እና አስተዳደር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተካሄደው የምክክር መድረክ ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቅቋል፡፡
አቶ ጥላሁን ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ ተደራሽነት እና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች ለረዥም ጊዜ የቆዩና ፈርጀ ብዙ ናቸው፡፡
በተለይ የፕሮጀክቶች ከፍተኛ የጥራት ችግር እና በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ከፍተኛ የጊዜና የሃብት ብክነት ሲያስከትል መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡
ይህም ክልሉን ለተጨማሪ ከፍተኛ ወጪ ሲዳርግ ከመቆየቱ በላይ ህብረተሰቡን ለአላስፈላጊ እንግልት በመዳረግ በክልሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ስርጭት ላይ የኢ-ፍትሃዊነት ጥያቄ ማስነሳቱን አብራርተዋል፡፡
በክልሉ፣ በዞኖችና በታችኛው መዋቅር ከፍተኛ የሆነ የሃብት የአስተዳደር ችግር መኖሩን ጠቁመው÷ ይህም የመሰረተ ልማት ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በፌዴራል መንግስቱ በከፍተኛ ወጪ የሚሰሩ የመንገድ፣ የመብራትና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ሳይመረቁ ለጥገና፣ ተገቢውን ግልጋሎት ሳይሰጡ ለስርቆት እንዲሁም ለብልሽት እና ውድመት መጋለጣቸውን አንስተዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የችግሩን ጥልቀት በማጤን ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የመሰረተ ልማት አቅርቦ፣ ስርጭት፣ ጥራትና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮችን በተደራጀ አግባብ በተቋማዊ ማዕቀፍ ለመፍታት በመስራት ላይ መሆኑን መግለጻቸውን የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ለዚህም ክልሉ የከተማና የገጠር መሰረተ ልማት ጉዳዮችን ከዕቅድ እስከ አፈጻጸም በባለቤትነት የሚከታተልና የሚመራ ተቋም በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ስር ማቋቋሙ ተጠቁሟል።