ዓለምአቀፋዊ ዜና

የዓለም ጤና ድርጅት ዴክሳሜታሰን መድሃኒት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ፅኑ ህሙማን ለማከም ጥቅም ላይ መዋሉን በበጎ መልኩ እንደሚመለከተው ገለፀ

By Tibebu Kebede

June 17, 2020

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዴክሳሜታሰን መድሃኒት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ፅኑ ህሙማን ለማከም ጥቅም ላይ መዋሉን በበጎ መልኩ እንደሚመለከተው የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

የዴክሳሜታሰን መድሃኒትን የመጀመሪያ ዙር ውጤት የኮቪድ 19 ፅኑ ህሙማን ህይወት ለመታደግ እንደሚስችል ድርጅቱ ገልጿል።

ድርጅቱ መድሃኒቱ በመተንፈሻ መሳሪያዎች (ቬንትሌተር) እና ኦክስጅን ድጋፍ የሚተነፍሱትን ታማሚዎች የመሞት እድልን የሚቀንስ መሆኑን የብሪታንያ ተመራማሪዎች ያወጡትን ውጤት እንደሚጋራም አስታውቋል።

ይህ መድሃኒት በፅኑ ህመም ላይ የሚገኙና በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎችን ለማከም እንደሚውል ያስታወቀው ድርጀቱ ህመሙ ላልጠናባቸው ሰዎች ግን አይመከርም ብሏል።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በኮቪ 19 ምክንያት በመተንፈሻ መሳሪያዎች (ቬንትሌተር) እና ኦክስጅን ድጋፍ የሚተነፍሱትን ታማሚዎች የመሞት እድል ለመቀነስ የሚያስችል የመጀመሪያው መድሃኒት መሆኑን ገልፀዋል።

የዴክሳሜታሰን መድሃኒት ከፈረንጆቹ 1960 ጀምሮ ለተለያዩ ህክምናዎች ጥቅም ላይ ሲውል እንደነበረም ነው የዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቀው።

ድርጅቱ የመጀመሪያውን የጥናቱ ውጤት እንደደረሰው በመግለፅ በቀጣይ ቀናትም ከመድሃኒቱ ጋር ተያይዞ ሙሉ ትንተና እንደሚያደርግ ነው የገለፀው።

መድሃኒቱን ለኮቪድ 19 መቼ እና እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም በቀጣይ አሳውቃለሁ ብሏል።