የሳዑዲ አመራሮችና ባለሃብቶችን ያካተተ ልዑክ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳዑዲ ዓረቢያ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ባለሃብቶችን ያካተተ ልዑክ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ሊያደርግ ነው፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ከሀገሪቱ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴዔታ አልባራ አልስከ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም፤ የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
በዚህም የተለያዩ የሳዑዲ ዓረቢያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ ሃላፊዎች እና ባለሃብቶችን ያካተተ ልዑክ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ተገልጿል፡፡
የታቀደውን የጉብኝት መርሐ ግብር ስኬታማ ለማድረግ በትብብርና በቅንጅት ለመስራት ውይይት መደረጉንም የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡
ጉብኝቱ በኢትዮጵያና ሳዑዲ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ጉድለቶችና ተግዳሮቶች በጋራ ፈትሾ መፍትሄ በመስጠት ግንኙነቱን ለማሳደግና ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ልዑክ እስከ 25 አባላት የሚኖሩት ሲሆን÷ ጉብኝቱ እስከ ቀጣዩ ሐምሌ ወር አጋማሽ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡