በክልሉ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለተመለሱ የተሃድሶ ስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለተመለሱ የሰላም ተመላሾች የተሃድሶ ስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አሻዲሊ ሃሰን÷ በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር ሳቢያ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን አጥተናል ፤በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠያ ቆይተዋል፤ በመሰረተ ልማቶች ላይ ያደረሰው ጉዳትም ከፍተኛ ኪሳራ ጥሎ አልፏል ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግስት በሰዎች ላይ የሚደርሰውን የሰላም እጦት ለመቀለስ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ አሻዲሊ÷በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ የሰላም ተመላሾች ከጦርነት ይልቅ ሰላምን አስቀድመው እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱት ትጥቅ አንግቦ ጫካ በመግባት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት መሆኑን ጠቅሰው÷በቀጣይ ለሀገር ሰላምና እድገት ማንኛውም ዜጋ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሃሩን ኡመር በበኩላቸው÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ለኢትዮጵያ ሰላም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተረድተው ለመጡ የሰላም ተመላሾች ያላቸውን አክብሮት መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የሰላም ተመላሾቹ መሪ አብደላ ኡስማን በበኩላቸው÷ ሰላም ለሀገር እድገት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸው የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ልማት እንደሚገቡ ተናረዋል፡፡