ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም መረጋገጥ በሙሉ ዝግጁነት ላይ ትገኛለች- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም መረጋገጥ በሙሉ ዝግጁነት ላይ ትገኛለች ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሞተራይዝድ ሻለቃ የደረሰበትን ዝግጁነት ደረጃ ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ሞተራይዝድ ሻለቃው በተባበሩት መንግስታት ስታንዳርድ መሰረት የተሟላና ለማንኛውም ተልዕኮ ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻላቸውን ገልጸዋል።
ለምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል ኢትዮጵያ በሙሉ ዝግጁነት ላይ መገኘቷ ለአፍሪካና ለቀጣናው ሰላም ካላት በጎ ፍላጎት የመነጨ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከአስሩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በተሟላ ዝግጁነት ላይ መሆኗን ለማረጋገጥ መቻላቸውንም ተናግረዋል።
ለሞተራይዝድ ሻለቃው ዝግጁነት የመከላከያ የሎጂስቲክስ ዋና መምሪያና የፌዴራል ፖሊስ የማይተካ ሚና እንደነበራቸው ያወሱት ኤታማዦር ሹሙ÷ ለስኬቱ አስተዋፅኦ ላደረጉ አመራሮችና ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ብርጌድ ሃሳብ አመንጪና መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት ዝግጁነታቸው የተረጋገጠው የሞተራይዝድ ሻለቆቹ ከወታደር፣ ከፖሊስና ከሲቪል የተውጣጡ ናቸው ተብሏል፡፡
በቅርቡ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ብርጌድ ከፍተኛ አመራሮች የሞተራይዝድ ሻለቃውን ዝግጁነት ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡