እንደ ሀገር በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዘርፍ እየተሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው – አለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ ሀገር በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዘርፍ እየተሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ያዘጋጀው የታዳሽ ሃይል ተሽከርካሪዎች ትግበራ ስትራቴጂ ሰነድ ዛሬ ለስትሪንግና ቴክኒካል ኮሚቴ ቀርቧል።
በዚህ ወቅት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ እንደሀገር በኤሌክትሪክ መኪኖች ዘርፍ እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች ነው፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በሀገር ውስጥ በስፋት ለማምረትና ለመገጣጠም እንዲሁም በዘርፉ የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎች እንዲቀጥሉ ተቋማት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ ሃሰን መሃመድ በበኩላቸው÷ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያዎች በሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲመረቱና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ከፖሊሲ ቀረጻ ጀምሮ የመሰረተ ልማት አቅርቦት እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ረገድ ግንባር ቀደም ከሆኑና ልምድ ካላቸው ሀገራት ተሞክሮ የሚወስዱበት ሁኔታ እንደሚመቻች መጥቀሳቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡