ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የአሰራር ስርዓት ደንብን አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የአሰራር ስርዓት ደንብ ለምክር ቤቱ ጉባኤ ቀርቦ በአሰራር ስርዓቱ ላይ ተጨማሪ ሀሳቦችንና ግብአቶችን በማከል አጽድቋል።
የምክር ቤቱ ስድስተኛውን የፓርላማ ዘመን፣ ሦስተኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ እንደቀጠለ ነው፡፡
በዚሁ ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር÷ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ወይም አያስፈልጋቸውም በሚል በሰጠው ውሳኔ ቅር ተሰኝተው ለምክር ቤቱ የሚቀርቡ ሕገ መንግሥታዊ አቤቱታዎች በጥልቀት እየተመረመሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም አፋጣኝ እልባት እየሰጠ ዜጎች ጥራት ያለውና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ አቶ ቴዎድሮስ ምህረት÷ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የተሰጡትን ሕገ መንግሥታዊ ሀላፊነቶች ለመወጣት የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው እንዳይጣስ አቤቱታዎችን እየመረመረ ምላሽ እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕግን መሰረት ያደረገ የአሰራር ስርዓት ደንብ መጽደቅ ጉባዔው ግልጽነት የተሞላበትና ተጠያቂነት ያለበት ዘመናዊ አግልግሎት ለመስጠት ያስችለዋል ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡