ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የሀገሪቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሄኮ ኒትዝሺከ አረጋገጡ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጀርመን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሄኮ ኒትዝሺከ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች የጋራ ፍላጎቶችን መሠረት ባደረገ መልኩ በወቅታዊ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ጀርመን የኢትዮጵያ ሁነኛ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን የገለጹት አምባሳደሩ÷ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በተመለከተ አብራርተዋል፡፡
ሄኮ ኒትዝሺከ በበኩላቸው ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው ወሳኝ ሚና ያላት ሀገር መሆኗንም ልዩ መልዕክተኛው ተናግረዋል።