በምትሠራበት ቤት የ2 ዓመት ሕጻንን የጠለፈችው ግለሰብ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤት ሠራተኛነት በምትሠራበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ሶሊያና ዳንኤል የተባለች የሁለት ዓመት ሕጻንን የጠለፈችው ግለሰብ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣች።
ተከሳሽ ሕጻኗን ጠልፋ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ከተማ ወስዳ በደበቀችበት ወቅት በቁጥጥር ስር መዋሏ ተገልጿል፡፡
የግራ ቀኝ ክርክሮችንና ማስረጃዎችን መርምሮ በተከሳሿ ላይ የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ነው።
በተጨማሪም ችሎቱ ከተከሳሿ ጋር የተሰረቀ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር በመግዛትና በመሸሸግ ወንጀል የተከሰሰ ሌላ ግለሰብ በ8 ወራት እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ÷ ተከሳሽ ቤዛዊት በቀለ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮቿ ጋር ሆና መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ሳሪስ አዲስ ሰፈር ኤልቤቴል አካባቢ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ከምትሠራበት መኖሪያ ቤት ሶሊያና ዳንኤል የተባለች የሁለት ዓመት ሕጻንን ጠልፋ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ከተማ መውሰዷ ተመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ እና ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረጉት ክትትልም በሱሉልታ ከተማ ለዚሁ ወንጀል በተዘጋጀ ባዶ ቤት ሕጻኗን ይዛ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር መዋሏ በክሱ ተብራርቷል፡፡
በዚህም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና አንቀጽ 590 ንዑስ ቁጥር 1 ለ እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 (ሠ) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፋለች በሚል በዋና ወንጀል አድራጊነት ለአካለ መጠን ያልደረሰችን ሕጻን በመጥለፍ ወንጀል ተከሳ ነበር።
እንዲሁም በሁለተኛው ክስ ግለሰቧ ከዚሁ መኖሪያ ቤት ሦስት የሞባይል ስልኮችን፣ ሁለት ግራም የወርቅ ሐብል እና በአጠቃላይ 32 ሺህ 100 ብር የሚገመቱ ንብረቶችን ሰርቃ መሰወሯን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 669 ንዑስ ቁጥር 2 (መ) ሥር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፋለች በማለት በከባድ የስርቆት ወንጀል ክስ አቅርቦባታል።
በተጨማሪም ተከሳሿ ሕጻን ጠልፋ በቁጥጥር ስር መዋሏ በመገናኛ ብዙኃን መረጃው ከተሰራጨ በኋላ የተለያዩ ስሞችን በመጠቀም በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ስትሠራበት ከነበሩ መኖሪያ ቤቶች÷ “ላፕቶፕ ኮምፒዩተርን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶች ተሰርቆብናል” ያሉ ግለሰቦች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ማጣሪያ ተደርጎ ማስረጃ ከተሰበሰበ በኋላ በተመሳሳይ በአምስት በከባድ የስርቆት ወንጀል ክስ ተመስርቶባት ነበር።
በሌላ በኩል ኃይለ ኢየሱስ ኮርጃ የተባለ ግለሰብ በአንቀጽ 669 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ አንደኛ ተከሳሽ ከሌላ የግል ተበዳይ የሰረቀችውን 53 ሺህ ብር ዋጋ ያለው ላፕቶፕ ኮምፒውተር የተሰረቀ ንብረት መሆኑን እያወቀ በ16 ሺህ ብር ከ1ኛ ተከሳሽ በመግዛትና በመሸሸግ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።
በዚህ መልኩ በዐቃቤ ሕግ የተመሰረተባቸው ክስ በችሎት በንባብ ከተሰማ እና የዕምነት ክህደት ቃላቸው ከተመዘገበ በኋላ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ተሰምቷል።
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ በቀረበባት ተደራራቢ ሰባት ክሶች ላይ ዐቃቤ ሕግ የተቆጠሩ 30 ምስክሮችንና 2 በኤግዚቢት የተያዙ ማስረጃዎችን ጨምሮ 8 ገላጭ ተንቀሳቃሽና የፎቶ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም በሁለቱም ተከሳሾች ላይ የቀረቡ የሰውና የሠነድ ማስረጃዎችን መርምሮ አንደኛ ተከሳሽ በተከሰሰችበት ተደራራቢ ሰባት ክሶች እንድትከላከል ብይን ሰጥቷል።
እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽ በቀረበበት አንድ ክስ ላይ የተሰሙ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል።
ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃን ለመጠባበቅ ከአራት በላይ ቀጠሮዎች የተሰጠ ቢሆንም፤ ተከሳሾቹ መከላከያ ማስረጃ አላቀረቡም፡፡
በተለይም አንደኛ ተከሳሽ መከላከያ ማስረጃ ማቅረብ እንደማትችል ለችሎቱ አስታውቃለች፡፡
ፍርድ ቤቱም መርምሮ አንደኛ ተከሳሽን በተከሰሰችበት ተደራራቢ ሰባት ክሶች ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸሟ መረጋገጡን ጠቅሶ የዕምነት ማጉደል ማስረጃዎችን በመያዝ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባታል።
ሁለተኛ ተከሳሽም ማስረጃ በተሰማበት በመሸሸግ ወንጀል በአንድ ክስ ብቻ በሌለበት ጥፋተኛ ተብሏል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን መርምሮ 1ኛ ተከሳሽ ያቀረበችውን 4 የቅጣት ማቅለያ በመያዝ ጥፋተኛ በተባለችባቸው ሁሉም ክሶች በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ወስኗል።
እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽ በሌለበት በመሸሸግ ወንጀል በ8 ወራት እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።
በታሪክ አዱኛ