በምሥራቅ ጉራጌ ዞን 4 ሴት ሕጻናት በደራሽ ውኃ ተወሰዱ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ ከለኪንዶ ወንዝ አራት ሴት ሕጻናት በደራሽ ውኃ መወሰዳቸውን የከተማ አሥተዳደሩ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በውኃ የተወሰዱት ሕጻናት ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 15 እንደሚገመት የቡኢ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ጽ/ቤት አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር መለሰ ተሰማ አስታውቀዋል፡፡
ሕጻናቱ ወደ ከለኪንዶ ወንዝ ለጸበል ብለው በሄዱበት ዛሬ ጠዋት በደራሽ ውኃ መወሰዳቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
የሁለቱ ሕጻናት አስክሬን መገኘቱን እና የቀሪዎቹን ለማግኘትም ፍለጋው ተጠናክሮ ቀጥሏል ማለታቸውን የቡኢ ከተማ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሕብረተሰቡ ልጆቹን እንዲቆጣጠር እና ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡