ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት የተጠረጠረው ግለሰብ ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር ዋለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና በማሰራጨት የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለፀ።
ተጠርጣሪው በአዲስ ከተማ ወረዳ 8 ሁለት ሱቆች በኢንተርኔት ቤት ሽፋን በሀገር ላይ ጉዳት ለማድረስ ሆንብሎ ሀሰተኛ ፓስፖርቶች፣ የጤና ምርመራ ውጤቶች፣ ሲ ኦ ሲና ሌሎች ሠነዶችን አዘጋጅቶ ለኅብረተሰቡ ለማሰራጨት ሲል መያዙ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በተጠርጣሪው መኖርያ ቤት በተደረገ ብርበራ በዝግጅት ሂደት ላይ ያሉ ሀሰተኛ የቀበሌ መታወቂያዎች፣ የፌደራልና ክልል የልደት የምስክር ወረቀቶች፣ የአየር መንገድ በረራ ትኬቶች፣ የተለያዩ ተቋማት የባለሙያዎች የምስክር ወረቀቶች፣ የግብር ከፋይ ሰርትፍኬቶች፣ የእጅ በእጅ ደረሰኞች፣ የትምህርት ማስረጃዎችንና ክብ ማህተሞችን መያዝ መቻሉ ታውቋል፡፡
ተጠርጣሪው ሀሰተኛ ሰነዶቹን ለማዘጋጀት ይጠቀምባቸው የነበሩ ሃርድ ዲስኮች፣ ላፕቶፖች፣ ሲዲዎች፣ ፍላሾች እና ሀሰተኛ ሰነዶችን ለማተም የሚያገለግሉ ጠንካራ ወረቀቶችን በኢግዚቢት መያዙንም ፖሊስ ጠቅሷል፡፡
ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ከተጠረጠሩት ግለሰቦች መካከል አንድ ተጠርጣሪ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን÷ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ፖሊስ ክትትሉን አጠናክሮ መቀጠሉን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡