Fana: At a Speed of Life!

25 ሰዎች ከሱዳን ግጭት ሸሽተው በባህር ሲጓዙ ሰጥመው ህይወታቸው ማለፉ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ሱዳን ሲናር ግዛት ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ግጭት ሲሸሹ የተሳፈሩበት የእንጨት ጀልባ ተገልብጣ ቢያንስ 25 ሰዎች በባህር ሰጥመው ህይወታቸው እንዳለፈ ተነግሯል።

የአስቸኳይ ድጋፍ ሰጪ ኃይል ወደ አካባቢው ሲገባ፣ ከአቡ ሁጃር ከተማ በምስራቅ በአል ዲባይባ እና ሉኒ መንደር የደረሰ የመስጠም አደጋ ሲሆን፥ ከ25ቱ ሟቾች መካከል አብዛኞቹ ሴቶች እና ህጻናት እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ተጎጂዎቹ ከአልዲባይባ መንደር የመጡ ሙሉ ቤተሰቦችን እንደሚያካትትም ተገልጿል።

በሱዳን ጦር ሃይሎች እና በፓራሚሊታሪ አስቸኳይ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል የተፈጠረው ግጭት ከተስፋፋ በኋላ ከ55 ሺህ 400 በላይ ሰዎች የሲናር ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውን ሲንጋን ለቀው መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አስታውቋል።

በፈረንጆች 2023 ሚያዝያ ወር አጋማሽ የተቀሰቀሰው የሱዳን ግጭት ቢያንስ የ16 ሺህ 650 ሰዎችን ህይዎት መቅጠፉን የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሱዳን ውስጥ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ከ7 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ወደ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚጠጉ ሌሎች ደግሞ ድንበር አቋርጠው ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸውን የመንግስታቱ ድርጅት አለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት በሰኔ 25 ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ የዘገበው ዥኑዋ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.