ከመጪው መስከረም ጀምሮ የግብርና ናሙና ቆጠራ ለማካሄድ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመስከረም2017 ዓ.ም ጀምሮ የግብርና ናሙና ቆጠራ ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የ2017 ግብርና ናሙና ቆጠራ ስትሪንግ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡
ሁሉም የግብርና ዘርፎች የሚያጠቃልለው የግብርና ናሙና ቆጠራ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያሏትን ሃብቶች በትክክል ለማወቅ ብሎም ለፖሊሲ ዝግጅት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)÷ቆጠራው በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የግብርና ናሙና ቆጠራ ከ22 ዓመት በፊት መካሄዱንም አንስተው÷በቀጣዩ ቆጠራ እርሻና የእንስሳት ሃብትን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ሃብቶች እንደሚካተቱ ጠቅሰዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከመስከረም 2017 ጀምሮ የሚካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ ከዚህ ቀደም ከተደረገው ሰፋ ባለ መልኩ እንደሚከናወን ነው ያብራሩት፡፡
ቆጠራው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምዕራፍ ሁለት አካል መሆኑንና ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ያለው ፋይዳ ጉልህ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የግብርና ናሙና ቆጠራው ከ2017 መስከረም ጀምሮ ለአንድ ዓመት እንደሚከናወን ጠቁመው÷ከዚህ ቀደም ያልተካተቱ እንደ በጋ መስኖ፣ የሌማት ትሩፋት እና የግብርና ማዘመን ስራዎች ይካተታሉ ብለዋል፡፡
ቆጠራው በሶስቱም የምርት ወቅቶች ማለትም በመኸር፣ በበጋ መስኖ እና በበልግ እንደሚደረግ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አነስተኛ ይዞታ ባለው አርሶ አደር፣ በኢንቨስትመንት የሚለሙ ሰፋፊ እርሻዎችና በማህበር የሚለሙ መሬቶችም ይካተታሉ ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ቆጠራው ለግብርናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱን አንድ ሶስተኛ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት የያዘ መሆኑን አንስተው÷በዘርፉ የሚመጡ ለውጦች ለሀገር ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡
ቆጠራው የግብርናው ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን አስተዋጽኦ ከመረዳት አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር)÷ለቆጠራው አስፈላጊውን ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በቆጠራው ከ62 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል፡፡
የ2017 የግብርና ናሙና ቆጠራ ስትሪንግ ኮሚቴን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና የግብርና ሚኒስቴር በበላይነት የሚመሩት ሲሆን÷ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ተካተውበታል፡፡