የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት 1 ሺህ 100 ተማሪዎችን አስመረቋል።
ከተመራቂ ተማሪዎች 671 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 397 የሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም 32 ተመራቂዎች ሦስተኛ ዲግሪ ያጠናቀቁ መሆናቸው ተገልጿል።
ከተመራቂዎቹ መካከል 18ቱ ደግሞ “የዱዋል ሜጀር” ወይም የጥምር ሙያ ተጠቃሚዎች ናቸው።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሳካት ትምህርትና ስልጠና ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት በጥራት ላይ የተመሰረተ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተልዕኮውን ለመወጣት እየጣረ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከጥናትና ምርምር ጀምሮ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና በማከናወን እንደሚታወቅ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሰቲዉ ልዩ ተልዕኮ ከተሰጣቸው ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በመሆን ስምንት የልህቀት ማዕከል ዩኒቨርሲቲዎችን ለመምራት ተመርጧል ብለዋል ።
የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የሀገሪቱን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ሊለውጡ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲስፋፉ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የተማሪዎች የፈጠራ ክህሎት እንዲዳብር የፈጠራ ክህሎት ማበልጸጊያ ማእከል ተከፍቶ ተማሪዎች እንዲሳተፉበት መደረጉን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከ90 በመቶ በላይ ተመራቂ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና አልፈዋል ተብሏል፡፡
በምንተስኖት ሙሉጌታ