Fana: At a Speed of Life!

የፈረንሳይ ከዋክብት የጎል ድርቅ በአውሮፓ ዋንጫ አዲስ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የላቀ ክህሎት ያላቸው ከዋክብትን የያዘው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በክፍት ጨዋታ አንድም ግብ ሳያስቆጥር ግማሽ ፍጻሜን በመቀላቀል አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡

ትናንት ምሽት ከ120 ደቂቃ ፍልሚያ በኋላ ፈረንሳይ ፖርቹጋልን በመለያ ምት 5 ለ 3 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፏ ይታወሳል።

የትናንት ምሽቱ ውጤት ለፈረንሳይ በድል አድራጊነት ይመዝገብ እንጂ ሀገሪቱ በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ የራሷ ተጫዋቾች ከክፍት ጨዋታ ግብ ሳያስቆጥሩ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያለፈች የመጀመሪያዋ ቡድን በመሆን አዲስ ክብረ-ወሰን አስመዝግባለች።

ሌላኛው አዲስ ክብረ-ወሰን÷ በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ እስካሁን በተደረጉት ሁሉም ጨዋታዎች ባልተለመደ መልኩ 9 ያህል ግቦች በራስ ላይ የተቆጠሩ ናቸው፤ከእነዚህ ውስጥም ሁለቱ ለፈረንሳይ ተመዝግበዋል፡፡

በብዙዎች ዘንድ ዋንጫውን ያሸንፋል የሚል ግምት የተሰጠው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ቢሆንም እስካሁን በሜዳ ላይ አሳማኝ አቋም ማሳየት አልቻለም፡፡

በምድብ ማጣሪያው ፈረንሳይ ኦስትሪያን 1 ለ 0 ስታሸንፍ የኦስትሪያው ተከላካይ ማክሲሚሊያን ቮበር በራሱ መረብ ላይ ያሳረፋት እና ቤልጂየም በ16ቱ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ በፈረንሳይ 1 ለ 0 ተሸንፋ ከውድድሩ ስትሰናበት የቤልጂየሙ አንጋፋ ተከላካይ ያን ቬርቶንኸን በተመሳሳይ በራሱ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡

በኪሊያን ምባፔ እና በአንቷን ግሬዝማን የሚመራው የአጥቂ ክፍል በአምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ያስቆጠረ ቢሆንም ግቡ የተገኘው ከፖላንድ ጋር በነበረው ጨዋታ ከፍፁም ቅጣት ምት ነው፡፡

በጥቅሉ እስካሁን ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ያስቆጠራቸው ግቦች በሙሉ በራስ ግብ የተቆጠረ (2) ወይም በፍፁም ቅጣት ምት (1) የተገኙ ናቸው።

ቡድኑ አሁን ላይ ወደግማሽ ፍፃሜ ለመድረሱ ግን የቡድኑ ጥብቅ የመከላከል አቀራረብ እንደሆነ በየጨዋታዎቹ ሒደት ታይቷል፤እስካሁን በአምስት ጨዋታዎች የተቆጠረበት አንድ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ብቻ ነው፡፡

በተለይም ታታሪው የመሐል ሜዳ ተጫዋች ንጎሎ ካንቴ ወደ ቡድኑ መመለሱ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

ፈረንሳይ ትናንት ምሽት ፖርቹጋልን በመለያ ምት መርታቷን ተከትሎ ካንቴ ለሀገሩ ተሰልፎ በተጫወተባቸው የአውሮፓ ዋንጫ እና የዓለም ዋንጫ 20 ያህል ተከታታይ ጨዋታዎች ባለመሸነፍ ብቸኛው አውሮፓዊ ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡

የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በግማሽ ፍጻሜው በአስደናቂ አቋም ላይ ከሚገኘው የስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

የስፔን ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች 11 ግቦችን ሲያስቆጥር ከነዚህ ውስጥ አስሩ በክፍት ጨዋታ ሒደት የተገኘ ሲሆን ÷ቀሪው አንድ ጎል ደግሞ አርሰናልን ሊቀላቀል ከጫፍ የደረሰው የጣልያኑ ተከላካይ ሪካርዶ ካላፊዮሪ በምድብ ማጣሪያው በራሱ መረብ ላይ ያስቆጠረው ነው፡፡

በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ከፈረንሳይ ቀጥሎ የተጠበቀውን ያህል መሆን ያልቻለው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንም እስካሁን በአራት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ብቻ አስቆጥሯል፡፡

ከዚህ ባለፈም እንደፈረንሳይ ሁሉ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡደን በሜዳ ላይ አሳማኝ የሆነ ብቃት ማሳየት አለመቻሉን ነው በርካቶች የሚናገሩት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.