ስፖርታዊ ውድድሮች አብሮነትን የማጠናከር ሚናቸው የላቀ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስፖርታዊ ውድድሮች በሕዝቦች መካከል ሰላምን፣ አንድነትና አብሮነትን የማጠናከር ሚናቸው የላቀ መሆኑ ተመላከተ፡፡
በጋምቤላ ክልል በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ”ሁሉም ለሰላም ሰላም ለሁሉም” በሚል መሪ ሐሳብ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።
በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው ውድድር ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ተወካይ አምቢሳ ያደታ እንደገለጹት÷ ስፖርት ሰላምን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን በማጠናከር ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
በክልሉ ያለውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ የሕዝቡን የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ለመስጠት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ገልፀዋል።
መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እያደረገ ላለው ጥረት መሳካት የሕዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ማስገንዘባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዛሬው የጎዳና ላይ ሩጫ ዋና ዓላማም ሕዝቡ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የሰላም ግንባት ሂደት ላይ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ለማነሳሳት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡