የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለማስፈተን በቂ ዝግጅት መደረጉን የጋምቤላ ክልል መንግሥት አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢሲ) የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ለማስፈተን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ፈተናውን ለመስጠት የተደረጉ ዝግጅቶችን በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ተመልክተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት አቶ ኡሞድ እንዳሉት በመጀመሪያና በሁለተኛው ዙር በተሰጠው ፈተና የተገኙ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ሰሞኑን ለሚጀምረው ፈተና የተሻለ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በዚህም ፈተናው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡
ተማሪዎች በግቢው በሚኖራቸው ቆይታም አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶች ተመቻችቶላቸዋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
ወላጆችም ከዛሬ ጀምሮ ተፈታች ልጆቻቸውን በወረዳ ማዕከል በተዘጋጀ የትራንስፖርት አገልግሎት አማካኝነት ወደ መፈተኛ ዩኒቨርሲቲ እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል።