ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፈል ሀገርን መገንባት ነው- አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብርን በወቅቱ እና በታማኝነት መክፈል ሀገርን ማልማትና መገንባት በመሆኑ የሚያኮራ የዜግነት ተግባር ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ ዓመታዊ የግብር መክፈያ ወቅትን በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ግብር የተጫነብን ሳይሆን እንደ ዜጋ ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን በመወጣት የምንፈጽመው የሚያኮራ የዜግነት ተግባር ነው ብለዋል፡፡
የሚጠበቅብንን ግብር በአግባቡ መክፈላችን እጅ ለእጅ ተያይዘን የውስጥ ገቢ አቅማችንን በማጎልበት በኅብረት የጋራ ልማታችንና ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን በፈጠነ ጊዜ ለማረጋገጥ ያስችለናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ግብርን በታማኝነት መክፈል ለራስና ለሀገር ክብር መሆኑን በመረዳት የክልሉ ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን የገቢ ግብር በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፍሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡