ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስቸጋሪ ፈተናዎችን በድል እየተወጣ እንደሚገኝ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድን ከጠቅላይ መምሪያዎች ጋር በመፈራረም ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሥራ መመሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል÷ ከለውጡ በፊት የነበሩ የአፈፃፀም ክፍተቶች ሪፎርሙ በፈጠረው ዕድል እየተስተካከሉ መምጣታቸው አንስተዋል፡፡
አሁን ላይም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሁሉም የሥራ ዘርፎች አጥጋቢ ውጤት እያስመዘገበ ከመምጣቱም በላይ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድን ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በማስጀመር ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሠራዊት በጠንካራ አመራር እየተመራ አስቸጋሪ ፈተናዎችን በድል እየተወጣ እዚህ ላይ ደርሷል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ጠንካራ የጋራ አመራር በመስጠት ተቋሙን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ ሁሉም አመራር መረባረብ እንዳለበት ጥሪ ማቅረባቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በማድረግና በመፈፀም አቅም እያደገ በሎጂስቲክስ አቅሙ ከፍ ወደ አለ ደረጃ የሚደርስበት ዓመት እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡
እቅዱ ተግባራዊ ከተደረገ የፖሊስ አገልግሎት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያድግና የተቀመጠው ራዕይ በአጭር ጊዜ እንደሚሳካም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር የዕቅዱን አስፈላጊነት በውል ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ ሌት ተቀን እንዲተጋ አሳስበዋል።