Fana: At a Speed of Life!

የሽንኩርት ዋጋ መናር ምክንያት የሆኑት ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 11 ፣2012 ፣(ኤፍ.ቢ.ሲ) የሽንኩርት ዋጋ መናር ምክንያት ላይ ጥናት በማድረግ ምክንያት ሆነው በተገኙ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እሸቴ አስፋው ÷በሚኒስቴሩ የሚመራው የገበያ ማረጋጋት ብሔራዊ ግብረ ኃይል የሽንኩርት ዋጋ ጭማሪውን አስመልክቶ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።

በጥናቱ መሰረት ለሽንኩርት ዋጋ  ጭማሪው የምርት እጥረት መኖሩ አንድ ምክንያት ቢሆንም ችግሩ በዋናነት የተፈጠረው ግን የሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ጣልቃ ገብነት መሆኑ ተረጋግጧል።

በመሆኑም ሽንኩርትና ቲማቲም የመሳሰሉ አትክልቶች የሃገር ውስጥ ፍላጎትን ሳያሟሉ ወደ ውጭ እንዳይወጡ ለሁሉም የጉምሩክ ጣቢያዎች ደብዳቤ በመፃፍ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

እስካሁን በተደረገው ክትትልም ምርቶቹ በሱማሌ ክልልና በድሬዳዋ በማቆራረጥ ወደ ጂቡቲ፣ ሱማሊያና ኬንያ እየተላኩ መሆኑ ተደርሶበታል።

ሕገወጥ ነጋዴዎች 11 መኪና ሽንኩርት ወደ ጅቡቲ ሲያስወጡ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አቶ እሸቴ ተናግረዋል።

በተጨማሪም አዳማ ላይ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና መሰል ምርቶችን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ የተያዙ ስለመኖራቸውም ጠቅሰዋል።

ከአሁን ቀደም በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የሽንኩርት ምርት ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ መቅረቱ የራሱ ተፅዕኖ እንደነበረውም አክለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በሱዳን በኩል የነበረው የሽንኩርት አቅርቦት የሚቀጥልበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አቅርቦትና ምርት ላይ የሚሰራው እንዳለ ሆኖ የኅብረተሰቡም ትብብር በመኖሩ ሕገወጥ ደላሎችና ነጋዴዎችን ወደ ሕግ የማቅረቡን ስራ እናጠናክራለን  ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.