ከውጭ ሀገራት ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ተልኳል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ከውጭ ሀገራት ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገለጸ።
የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አጥላው እንደገለጹት÷ ባለፉት አምስት ዓመታት ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር ቤት የሚላከው ገንዘብ (ሪሚታንስ) ጨምሯል።
በዚህም በ2016 በጀት ዓመት በሪሚታንስ ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት መላኩን ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል 273 የዳያስፖራ አባላት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ለማስቻል ተጨባጭ ሥራዎች መሰራታቸውንም ጠቁመዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 50 የዳያስፖራ አባላት ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ 3 ሺህ የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
ጎን ለጎንም ዳያስፖራው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎች ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በቀጣይም የዳያስፖራ አባላት በተለያዩ መስኮች የሚያደርጉት ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡